የሀዋሳ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያ ታሪክ ባጭሩ

የሀዋሳ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያ ታሪክ ባጭሩ

የሀዋሳ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን (ሀሙወአቤክ) ጅማሬ የሁለት ክስተቶች ድምር ውጤት ነው ። ዋነኛው ከሀዋሳ በ45 ኪ.ሜ. ላይ በምትገኝ በይርጋ ዓለም ከተማ የነበረችው የሙወአቤክ አጥቢያ ላይ በ1971 ዓ.ም የደረሰው ስደት ነበር፡፡ በዚህ ስደት ሦስት የቤተ ክርስቲያንዋ ወንጌላውያን (የምዕመናኑ መሪዎች ሆነው ያገለግሉም የነበሩ) እና ሌሎችም ዘጠኝ ወንድሞችና አራት እህቶች በጊዜው በነበረው የኢትዮጵያ ሶሻሊስት/ኮሚዩኒስት አምባገንን መንግስት ወደ ወኅኒ ሲጣሉ በከተማው ከነበሩት የቤተክርስቲያን አባላት መካከል ጥቂት የማይባሉ ወደ ሀዋሳ መፍለስ ግድ ሆነባቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ቀደም ሲልም ጀምሮ በሥራና በሌሎች ምክንያቶች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ሀዋሳ ከተማ የመጡ የሙ/ወ/አ/ቤ/ክ አባላት ነበሩ። በነዚህ ሁለት ምክንያቶች ወደ ሀዋሳ የመጡ ወገኖች ናቸው ለሀሙወአቤክ ጅማሬ ምክንያት የሆኑት።

እነዚህም ቅዱሳን በትናንሽ ቁጥር በየመኖሪያ ቤቶች በስውር እየተሰበሰቡ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠኑና ሲጸልዩ አንዳንዴም በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በጋራ ሲያመልኩ ቆይተው በ1978 መጨረሻ ገደማ በወኅኒ የነበሩ አገልጋዮችና ሌሎች ወገኖች ከእስር ሲፈቱ ሁኔታዎች ተለውጠው ከቀድሞው ይልቅ የተደራጀ ህብረት ተመስርቶ በተለያዩ ቦታዎች መንፈሳዊ ፕሮግራሞች መደረግ ጀመሩ። የወንጌል ስርጭትም ተጠናክሮ ቀጠለ። የሚድኑትም እየተጨመሩ በዙ። በመጨረሻም በግንቦት 13 ቀን 1981 ዓ.ም የሀዋሳ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን (ሀ/ሙ/ወ/አ/ቤ/ክ) ራስዋን የቻለች አጥቢያ ሆና ተመሰረተች፤ በተመሰረተችም በዓመቱ በ1982 ዓ.ም የቤተእምነቱ ማለትም የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን አባል ሆነች።

ቤተክርስቲያንዋ በህቡእ የተደራጀች በመሆንዋ የራስዋ መሰብሰቢያ ሕንጻ አልነበራትምና አስቀድሞ ሀዋሳ የሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ አንድ ክፍል ተፈቅዶላት በሳምንት አንድ ቀን ፕሮግራም ይደረግ ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ ከይርጋ ዓለም፣ ከዲላና ከየአካባቢው ከሚመጡ የሙሉ ወንጌል ምዕመናን ጋር በግምቤ ገነት ቤተ ክርስቲያን ለጌታ እራት አልፎ አልፎ ለመገናኘትና ለመዕናናት ተችሏል።  ይህም ሁኔታ ዘላቂ ሆኖ ባለመገኘቱ በ1983 ዓ.ም አንድ ሙሉ ግቢ በኪራይ ተገኝቶ የተለያዩ መደበኛ ፕሮግራሞች መካሄድ ጀመሩ። በ1986 ዓ.ም ለቤተክርስቲያንዋ ከመንግስት በተፈቀደ ቦታ (በአሁኑ የሀሙ/ወ/አ/ቤ/ክ ግቢ ውስጥ) የመጀመሪያው የቤተክርስቲያንዋ መሰብሰቢያ መጠለያ ተሰርቶ መደበኛ አምልኮ መካሄድ ተጀመረ።

የሀሙወአቤክ ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው አጠቃላይ ሁኔታ በመነሳት ቤተክርስቲያኒቷ ራስዋን የቻለች አጥቢያ ሆና ከተመሰረተችበት 1981 ዓ.ም. ጀምሮ በ31 ዓመታት ውስጥ ከሀዋሳ ከተማ ውጭም ጭምር  አገልጋዮችን  በመላክ በየቦታው ያደራጀቻቸውን ጨምሮ ዛሬ (በ2012 ዓ.ም) ራሳቸውን በቻሉ በ262 አጥቢያዎች የተደራጀች ቤተክርስቲያን ሆናለች።

በአጠቃላይ የሀሙወአቤክንን ጅማሮና እድገት ስንመለከት በስደት ዘመን ተወልዳ በመከራ እሳት ውስጥ አልፋ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አሁን ላለችበት ደረጃ የበቃች ጠንካራ ቤተክርስቲያን መሆንዋን እንገነዘባለን።

ክብሩ ሁሉ ለእግዚአብሔር ይሁን !!!

 

Quick Contact!

  • TEL +251-46 220 5433
  • TEL  +251-46 220 5563
  • MOB: +251-902-50-44-44
  • Emai: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.hfgbc.org
  • WEB: www.hawassafullgospelch.org
  • Address: Hawassa, Ethiopia

Weekly Programs

Program will be listed here

Newsletter

Stay up To date with our newsletter.